Saturday, May 31, 2014

የኋልዮሽ ጉዞ

                                                                                                                                         

መጋቢት  ወር  ነው።  የፋክት  መፅሔትን  ቅፅ  2  ቁጥር  37  እያነበብኩ።  ፕሮፌሰሩ  (/  መስፍን /ማሪያም)  “መጠላለፍ  ወደየት  እየመራን  ነው?”  በሚል  መጠይቅ  የፃፉት  ፅሁፍ  እንደኔ የሃይማኖንቶችን  መቻቻል፣  መፈቃቀር፣  መረዳዳትና  መከባበርን  ልምዱ  አድርጎ  ላደገ ኢትዮጵያዊ ያስደነግጣል፤ ያስፈራል። ፕሮፌሰሩ በፅሁፋቸው ካነሷቸው ሃሳቦች ካንዱ በስተቀር ሌሎቹን የተለያየ ቦታ  ስላነበብኳችው  ቢያስፈሩኝም  አዲሴ  አልነበሩም።  እንደሚከተለው  የገለፁት  ግን  ለኔ  አዲሴና በጣምም ውስጤን የነካኝ ነበር።
“…  አሁን ደግሞ  ሌላ ማዘዣ  ሰማሁ፤  የስ  የሚለው  የውሃ  ጠርሙስ  ላይ  እንስራ  የተሸከመችው ኮረዳ  መስቀል  አድርጋ  ነበር፤  ልጅቱ  ከነ  መስቀሏ  የምትታይበትን  ውሃ  እስላሞች  አንገዛም ስላሉ  ነጋዴዎች  መስቀሉን  አወለቁባትይህንን  ማዘዣ  ላወጣው  አክራሪ  እስላም  ወረባቦ ቅዳሜ ገበያ ሄዶ እንዲጎበኝ አሳስበዋለው፤ ዛሬ ተለውጦ እንደሆነ አላውቅም እንጂ እኔ ብዙ ግዜ ተመላልሼ እንዳየሁት የወረባቦ ኮረዶች ሁሉ ትልልቅ መስቀል በአንገታቸው ላይ ይታይ ነበር፤ መስቀል የእምነት መገለጫ ይሆናል፤ አያጠራጥርም፤ ግን መስቀል ጌጥም ይሆናል! ...”

እኔም በግሌ የታዘብኳችቸው ነገሮች ስለነበሩ የፕሮፌሰክሩን ሃሳብ ተጋራዋቸው። ወረባቦ ባልሆንም ተመሳሳይ  ባህል  ባለው  ማህበረሰብ  ውስጥ  ስላደኩ  ሃሳባቸውን  ለማጠናከር  ፈለኩ።  ግን  ፀሃፊ አይደለሁም።  ሃሳቡ  ከሳምንታት  አልፎ  ወደ  ወራት  ተሻገረ።  ተመሰሳሳይነት  ያለው  ሃሳብ  ከቀናት  በፊት ከጓደኞቼ  ጋር  ተወያየን።  ዛሬ  ግን  ፀሃፊ  ባልሆንም  ስለሚያገባኝ  ብቻ  የሆነ  ነገር  ማለት  እንዳለብኝ ተሰማኝ። መልካም ንባብ! አስታውሱ ፀሃፊ አይደለሁም።

እድገቴ በግምት 95% ሙስሊም 5% ክርስቲያን (ኦርቶዶክስ) የሆነ ማህበረሰብ ባለበት ደቡብ ወሎ ዉስጥ  ከሚገኝ  ባንደኛው  መንደር  ነው።  በሃይማኖቴ  ሙስሊም  ነኝ።  ቁጥሩን  ዝም  ብዬ አልቆጠርኩትምማለቴ  95/5! እደግመዋለው  95% ሙስሊም  5% ኦርቶዶክስ  ክርስቲያንቁጥሩን በልባችሁ ይዛችሁ ባከባቢዬ ስለተለመደ ባህሎችና ልማዶች ጥቂቶቹን ላውራችሁ።

ከማን  ልጀምር? ከሃምሌ  ልጀምር  መሰለኝ  -  አዎ  ከሃምሌ።  ያኔ ልጅ እያለው  ከዛሬ  9/10 ዓመት  በፊት ክረምቱ  መግባቱን  ካበሰረ  በኃላ  የኔና  የኩዮቼ  የመጀመሪያ  ስራ  የሚሆነው  ጅራፍ መግመድ  ነው  -ጅራፍ።  ጅራፍ  ማጮህ።  ከጋራ  ጋራ  ሆኖ  ከጓደኛ  ጋር  መፎካከር፣  ጓደኛን  በግጥም  ማሞገስ  ወይም መስደብ
“…እከሌ ነህ ወይ
እከሌ ነህ ወይ
ቁና በርበሬ ላበድርህ ወይ
ያችን ስትበላ አንዴ ቂጥህ ላይ
ልቆንድድህ ወይ
ውይይይይ…” (ጅራፉ ይጮሃል)
ፍየሎችን እየጠበቁ ትንሽ ጎጆ ቤት መስራት።  የነሃሴ 13 ለታ ሙልሙል ዳቦ መብያ ጎጆ ቤት። ነሃሴ 13  መቼም  ታውቁታላችሁ  -  ቡሄ  ነው።  አስቡት  ቡሔ  ሃይማኖታዊ  በዓል  ነው  -  የኦርቶዶክስ  እምነት ተከታዮች።  እኔም  ሆነ  ጉዋደኞቼ  ግን  ኦርቶዶክስ  አልነበርንም።  ማንም  ስለሃይማኖታዊ  በዓልነቱ የነገረንም አልነበረም። እኛም በደስታ አክብረነዋል። ዛሬ ግን ከዓመታት በኃላ ወደ መንደሬ ስመለስ ጅራፍ  አይጮህም፤  ዳገት  ጎጆ  አይሰራም፤  የቡሄ  ለታ  ልጆች  ሙልሙል  በጎጆ አይበሉም።  ለምን ብላችሁ ብጠይቋችው፤ እንዴ የአማራ (የክርስቲያን ለማለት ነው) በዓል እኮ ነው ይሏችኋል።

ቡሄ  ተበላ፤  አልቃሽ  ቡሄም  በማግስቱ።  ዝግጅት  ለቀጣይ  በዓል…!  የከሴ  እንጨት    ዲጊጣና  (  የተክል አይነት  ነውየላጫ  ተክል  በቀጫጭኑ  መሰንጠቅ    የባህር  ዛፍ  ልጥ  የጥድ  ልጥ  ከቤት  ጣራ  ላይ መጣልማድረቅሽር ጉድ እስከ ዘመን መለወጫ ዋዜማ!
“…የጎመን ዘመን ውጣ
የገንፎ ዘመን ግባ…”
የዋዜማው  ለታ  ውይ  ወይ”( ‘ውይ  ውይ’  በማህበረሰቡ  ችቦ  ለማብራት  የተሰጠ  ስያሜ  ነው። ስያሜውን  ያገኘው  ልጆች  ችቦውን  ሲያበሩ  ከግራ  ወደ  ቀኝ፣  ከቀኝ  ወደ  ግራ  ውይም  የክብ  ቅርፅ እየሰሩ  ችቦውን  እየወዘወዙ  “ውይ  ውይ”  እያሉ  ስለሚጮሁ  ነው።)እኔ  ከዛ  ማህበረሰብ  እስከምወጣ ችቦ  ማብራት  ለኦርቶዶክስ  እምነት  ተከታዮች  ብቻ  የተፈቀደ  መሆኑን  አላውቅም  ነበረ።  ዛሬ  ላይ  መንደሬ  ጎራ  ብትሉ  ያንን  ሁላ  ግርግር  አታገኙም።  ለምን  ብላችሁ  ብትጠይቁ  የአማራ  በዓል  ነው የሚል ምላሽ ታገኛላችሁ።

ዘመን  መለወጫ  አለፈ።  አሁንም  ግን  ዲጊጣ፣  ላጫ፣  ባህር  ዛፍ  ቅርፊት፣  ፅድ  ቅርፊት፣  ከሴ  … ቤት ጣራ ላይ መጣልማድረቅችቦ መስራትይቀጥላል - እስከ መስከረም 16 ለመስቀል ዋዜማ! የዛለታምውይ ውይአለ። ውይ ውዩን ተከትሎሆያ ሆዬ
“…ሆያ ሆዬ
ሆያ ሆዬ
የኔማ እገሌ
የሰጠኝ ሙክት
ግንባረ ቦቃ
ባለ ምልክት…”
ሆያ  ሆዬን  እዚህ  ምን  አመጣው  ነው  ያላችሁትአዎ  ሆያ  ሆየ  እዚህ  መቷል።  እንደዛሬው  ውይ ውዩም ሆያ ሆየውም የኦርቶዶክስ ብቻ ሆኖ ሳይቀር  ሙስሊም ማህበረሰብ ሆያ ሆዬ የሚለው ለመስቀል ነበረ።

ቋሚ  የሆነ  ጊዜ  ስለሌላቸው  ኢድ  አልፈጥርን(የፆም  ፍችእና  ኢድ  አልድሃን  (አረፋእዚህ  ጋር ልጨምራቸው  መሰለኝ።  የበዓሉ  ግዴታ  የሆነውን  ሰላት  ለመስገድ  ወደ  አከባቢው  ወደሚገኘው የአንደኛ  ደረጃ /ቤት  ኳስ ሜዳ  95% ህዝበ  ሙስሊም  ሲያመራና መዳ ውስጥ  ገብቶ ሲሰግድ  5%  ህዝበ ክርስቲያን ሜዳዋን ከቦ ሰላቱ እስከሚያበቃ ይጠብቃል። ሰላቱ እንዳበቃ ዝክር እየተዘከረ ወደ መስጊድ ሲኬድ ቁጥራችው ትንሽ ቢሆንም ዝክሩን የሚያደምቁት ክርስቲያኖቹ ነበሩ። ዛሬ ግን ምን እንደፈጠረ  ባላውቅም  ድምቀታቸው  ፈዟል።  ሳስበው  ክርስቲያኖቹ  የኢቲቭን  ቃል  የተዋሱ ይመስለኛል - አሸባሪ!

ታህሳስ  ወሩ  ከገባ  ጀምሮ  ጉድ  ጉድ  ለሌላ  ደስታከቂጡ  ቆልመም  ያለ  ዱላ  (ገና፣ጥንግ  (ከቀለጠ ፕላስቲክ  የተሰራ  የቴነስ  ኳስ  ቅርፅና  መጠን  ያለው  ኳስ  ቆሊ  (ከእንጨት  የተሰራ  የቴነስ  ኳስ ቅርፅርና  መጠን  ያለው  ኳስ)  …ማዘጋጀት…  እስከ  ታህሳስ  28/29  ድረስ…  ፀሃይ  ወደ ምዕራብ  አቅጣጫ ስታደላ ጀምሮ ብርሃኑ ላይን እስኪይዝ ድረስ ገና መጫወት። ጥንጓ ወይም ቆሊዋ ከሆተች (በኳስኛ ቋንቋ ጎል ከገባ) በኃላ መጨፈር
“… ሰሌ
ሃይ ገዳ
ገዳ
ሁጥቁሮን “xx” (ባለጌ ስለሆነ ነው)
…”
አስተውሉየልጅ  ነገር  ሆኖ  ነው  እንዳትሉ።  ገናውን  የሚጫወቱት  ልጆች  ብቻ  አይደሉም  ወጣትና ጎልማሶችም  ጭምር  እንጂ።  የታህሳስ  28/29  ለታ  አዛውንቶች  ተሰብስበው  ልጆቹንም  ወጣቱንም ጎልማሳውንም  መርቀው የወሩ ጨዋታ  ማለቁን  ሲያበስሩ  ልጃ  ገረዶች በመረዋ ድምፃቸው  ዜማውን ሲያንቆረቁሩት ጎረምሶች ደግሞ በጎርናና ድልቂያቸው በዓልሉን ያሳርጉት ነበረ። ዛሬ ገና የለም፤ ቆሊ የለም፤  ጥንግ  የለም፤  መረዋ  ዜማ  የለም፤ጎርናና  ድልቂያ  የለም፤ የሽማግሌዎች  ምርቃት  የለም!… በሱ ፋንታ እስከዛሬም በማድረጋቸው አምላካቸውን ይቅርታ እየጠየቁ ነው።

ማን  ነበረ  ከገና  ቀጥሎ  የሚመጣው  በዓል?  -  አዎ  ጥምቀት! “ለጥምቀት  ያልሆነ  ቀሚስ ይበጣጠስ”  የሚለው  ተረት  ለኦርቶዶክስ  እምነት  ተከታዮች  ብቻ  ሊመስላችሁ  ይችላል  - አይደለም።  እኔ  ባደኩበት ማህበረሰብአይደለም።  የጥምቀት  ዋዜማ  ለታ  ታቦቱን  ከቤተ ክርስቲያን  ወደ  ጥምቀተ  ባህሩ፣ በጥምቀተ  ባህሩ  ቦታ  ከታቦቱ  ጋር  አዳር፣  የጥምቀት  ለታ ከጥምቀተ  ባህሩ  ወደ  ቤተ  ክርስቲያንና የሚካኤል  ለታ  ሚካኤልን  ወደ  ቤተ  ክርስቲያኑ የሚመልሰው  5%  ኦርቶዶክስ  ብቻ  መስሏችሁ  ከሆነ ተሳስታችኋል።  ህዝበ  ሙስሊምም  አብሮ እንጂ።  ካለነሱ  በዓሉ  አይደምቅም  ነበራዛሬ  ግን  ቀዝቅዟል።የክርስቲያን  ታቦት  ልሸኝ  እንዴ”  የሚል  አስተሳሰብ  ባለው  ትውልድ  ስለተተካ  አዎ  ዛሬ  በዓሉ ቀዝቅዟል!

በሃገራችን የመውሊድን በዓል ከሚያከብሩ መስጂዶች የመጀመሪያውን የሚይዘው ጀማ ንጉስ ነው። ጀማ  ንጉስ  እኔ  ካደኩበት  መንደር  30  ደቂቃ  የእግር  መንገድ  ርቀት  ላይ  የሚገኝ  መድጂድ  ነው። በየአመቱ  በዓሉን  ለማክበር  በትላልቅ  ሺዎች  የሚቆጠር  ህዝብ  ከመላው  ሃገሪቱ  እንደሚመጣ አውቃለው።  በርካታ  ቁጥር  ያላቸው  ክርስቲያኖች  በዓሉን  ይታደሙ  እንደነበረም  አውቃለው።  ዛሬ ላይ ግን በዓሉን ከታደምኩ ረዥም ግዜ ስለሆነኝ እርግጠኛ አይደለሁም።

ይኝህ  እኔ  ያደኩባቸው  ማህበረሰብ  ክርስቲያኖች  ሙስሊሙ  መስጂድ  ሲሰራ  ድንጋይ  ፈልጠዋል፤ ድንጋይ  አግዘዋል፤  እንጨት  ቆርጠዋል፤  እንጨት  አግዘዋል፤  መዋጮ  አዋተዋል። ሙስሊሞቹም  ክርስቲያኖቹ  በተ/ክርስቲያን  ሲሰሩ  ተመሳሳይ  ነገር  አድርገዋል።  ዛሬ  ላይ  በመጠኑም  ቢሆን ጠብቀዋችው የያዟቸው በሃዘን በደስታ  በበዓል አብሮ  ማዘን መደሰት  መብላት መጠጣትን  የመሳሰሉ ታላቅ  ማህበራዊ  እሴቶች  ነበራቸው።  ሃዘንና  ደስታን  መጋራት  ማለቴ  ከሃይማኖታዊ  ስርዓት  ዉጪ ዛሬ  ላይ ቢኖርም እነሱንም ነገ ላለማጣታችን እርግጠኛ አይደለሁም።

ልጅነቴን  ሳስታውስ  ወደ  አዕምሮዬ  የሚመጡት  የቡሄ  ጅራፍ፣  የቡሄ  ጎጆ፣  የቡሄ  ሙልሙል፣ የንቁጣጣሽ  ዉይ  ዉይ፣  የመስቀል  ሆያ  ሆዬ፣  የኢድ  አልፈጥር  ዝክር፣  የኢድ  አልድሃ  ዝክር፣ የመውሊድ  ዝክር፣  የገና  ጨዋታ፣  የጥምቀት  ጭፈራ…  ናቸው።  ደስ  የሚሉ  ጣፋጭ  ትዝታዎች።  በዛ ማህበረሰብ  ውስጥ  አድጌ  ለዛ  እድል  በመብቃቴም  ደስተኛ  ነኝ።  ዛሬ  ግን  አዝኛለው።  እኔ  ያለፍኩበትን ዛሬ  ላይ  ያሉት  ልጆች  አላለፉበትም።  ዘመን  እየተለወጠ  አለም  መቶ  ሺህ  እርምጃዎች  ወደፊት ስትሮጥ፣  እንደኔ  አስተሳሰብ  ማህበራዊ  ህይወታችንና  አስተሳሰባችን  በሚሊዮኖች  መጨመር  ነበረበት። በተቃራኒው  ግን  ጉዟችን  የኋልዮሽ  የሆነ  ነው  የሚመስለው።  ምክንያቶች  እየፈለግን  ከሃይማኖትና ከብሄር  ጋር  እያስተሳሰርን  የሰይጣን  መለክተኛ  ለመሆን  ወደኃላ  እንሮጣለን።  እርግጥ  ነው  ዛሬ  ላይ ስለ  ሃይማኖትና  ብሄር  ኢትዮጵያ  ውስጥ  በግልፅ መወያየት  እንደተጠመደ  ፈንጂ  ያስፈራል።  እነሱ እየሄዱበት  ያለው  መንገድ  ደግሞ  ከፈንጁ  በላይ  ያስፈራል።  ግን  ዛሬም  አልረፈደም  ማውራት እንችላለን። 21ኛው /ዘመን ልጆች ነን እና።

ወደ  ፅሁፌ  ማጠቃለያ  ስመጣ  እንደዚህ  እጅና  ጓንት  ሆኖ  የኖረን  ማህበረሰብ  በሃይማኖት  ሰበብ ለመለያየት የሚደረግ ፅንፈኝነት ከየት የመጣ ነው? ከሱስ የሚገኘው ትርፍ ምንድነው? ቆይ የስ ላይ ያለችው  ባለ  መስቀል  ሴት  ውሃውን  ምን  አደረገችውያስቃልመስቀልንስ  የክርስቲያን  ብቻ ያደረገው ማነውአደራችሁን  እኔ  ሃይማኖት  እየተነተንኩ  አይደለምየስ  ውሃ  ላይ  ያለችውን  ከሚመስሉ ሙስሊም ኮረዶች (እንስቶች) ጋር ነው ያደኩት። በዛ እኔ ባደኩበት ማህበረሰብ ሴት ልጅ ከዳዴ ቀና ብላ በእግሯ መቆም ስትጀምር ከድንብልና ከቡዳ መድሃኒት ጋር አብሮ የሚታሰርላት መስቀል ነው። አስታውሱ እሷ ሙስሊም ናት። ለሃይማኖት ሳይሆን ለጌጥ ነው የታሰረላት።
ሃይማኖት  የግል  ነው  ይላል  ህጉአዎ  የግል  ነውሃይማኖታችንን  ለግል  እናድርገው! ሃይማኖታችን ተዋዶ፣  ተቻችሎ    ተረዳድቶና  ተከባብሮ  የኖረውን  ማህበራዊ  ህይወታችንን  እንዲፈታተንብን አንጠቀምበት።  ሃይማኖታዊ  ስርዓት  ቢሆኑም  በህብረተሰቡ  እንደ  ባህል የተያዙትን  ልማዶች  ሲሆን አዳብረን  አልያም  እንደነበሩ  እንያዛችው።  የፅንፈኝነት  ታርጋ  ለጥፈንላችው  ውበታችውን  አናጉድፍባቸው። በምድር ላይ ሃይማኖትን በማህበረሰብ ውስጥ ያለን አንድነት እንዲከፋፍል ወይም እንዲሸረሽር የሚሰብክ አስተምሮት አልነበረምም! የለምም! አይኖርምም!
©በእኔ   ነኝ 


 

No comments:

Post a Comment