Wednesday, June 25, 2014

እግር ወዶ

አይኔ:-
   አይኗን ጥርሷን ከናፈሯን፣
   ጡት ወገቧን ዳሌ ሽንጧን፣
   አድንቆላት ጎምዥቶላት፣
   ቁልቁል ወረደ፣
   ቁልቁል ነጎደ፣
   እግሯ ሲደርስ ፈዞ ቀረ፣
   ለመመልስ ተቸገረ፣
  አቤት ባቷ ተረከዟ
   አቤት ውበት የጣቶቿ፣
    ሲል ሲለፍፍ ሲመሰክር፣
    ስለ ውበታቸው ሲዘምር፣
    ሄዷል ለካ ብዙ ርቆ፣
    ላልጠፋ አካል እግር ወዶ።
  --------------------------------------
  ተፃፈ ላንቺ (G) 2002 ዓ.ም     
         ©እኔ ነኝ


Saturday, June 21, 2014

እድለቢስቷ

ለስለስ ያለ ንፋስ
           ሽው ሽው ሽውሽውሽው፣
አዋጅ መዓዛዋን ሲያዋህደው፣
የንብ መንጋ
          ዠበብ ዠበብ ዠበበብ ፣
እርፍ ቅስም
          ቅስም ቅስም ቅስምስምስም፣
ማር ስርት የሚጥም፣
ውብ ቢራቢሮዎች
           ብርር ብርር ብርርር፣
ማራኪ ህብር ፍጥር፣
ሲያደርጉ ማየት ነበረ ምኞቷ፣
ያልፈካችው ለጋ እምቡጢቷ፣
  ግና ግና
      በለስላሳው ፋንታ አውሎ ንፋስ፣
     ንቦቹን በዝንብ ጭርንቁስቁስ፣
     ቢራቢሮዎቹን በትንኝ ግብስብስ፣
     ተፈጥሮ ተካችና፣
የምቡጢቷ፣ 
   መዓዛዋ ገማና፣
   ውበቷ ቆሸሸና፣
   ምኞቷ መከነና፣
   ቅረች መና፣ 
   ያልተመረቀላት ፍካቷ፣
   እድለቢስቷ!
==================
     ©እኔ ነኝ